የተለየ አዲስ ለመስራት ሳይሆን ለአመታት ብዙ ተማሪዎችን ያስመረቀው የፋሲለደስ ት/ቤት ህንፃ በማርጀቱ የትምህርት ገበታ ላይ ባሉ ተማሪዎችና መምህራን እላያቸው ላይ ይናዳል የሚል ሥጋት በመፈጠሩ፣ በተጨማሪም በዚህ ሥጋት ምክንያት አንዳንዶች ህንጻዎች ለአገልገሎት እንዳይውሉ መታገዳቸውን በመመልከት፣ ትውልድ አሻጋሪ የሆነው ትምህርት ተጓጉሎ ትውልድ ወደኋላ መቅረቱ ያሳሰባቸው ተቆርቋሪዎች ት/ቤቱን በአዲስ መልክ ለመሥራት፣ የከተማው ነዋሪ ዜጎች፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ባለሙያተኞች እናም ሌሎች ተቆርቋሪዎች፣ ከሀገር ውጭ ደግሞ በፋሲለደስ መረዳጃ ማህበር ስር የተደራጁ ዜጎች ተነጋግረው አስፈላጊው ጥናትና መዋቅር ከተዘጋጀ በኋላ፣ በውጭ አገር ግን የት/ቤቱን ሥራ በሚመለከት ከፋሲለደሰ መረዳጃ በላይ ሰፋ በማለት አዲስ አሰተባባሪ ቡድን በማዋቀር እንቅስቃሴ ተጀመረ፡፡
ሌላው ከት/ቤቱ ሥራ ጋር በተያያዘ፣ ያረጀውና የፈረሰው ህንፃ በአጠቃላይ እያደገ ለመጣው የተማሪዎች ቁጥር በቂ አገልግሎት መሥጠት እንደማይችልም ግልፅ ነበር፡፡ ባረጀው ሀንጻ በአንድ ክፍል ውሥጥ አስከ ዘጠና ተማሪዎች በመጨናነቅ የትምህርት ጥራቱ እንደተጓደለም ግልፅ ነበር፡፡ ሰለዚህ አዲሱ የታለመው ህንጻ ይህንን ችግር እንዲቀርፍ ታስቦ ነበር መሠረት የተጣለው፡፡
በግልፅ፣ ይህ ዕዳ የተጣለው በከተማው ህዝብ ላይ ነበር፡፡ የወቅቱ መንግስት ጉዳዩንም አልተመለከተም፣ ለመርዳትም አልተግደረደረም፡፡
ከአራት አመታት በፊት የተጀመረው ይህ ፕሮጀክት፣ ከተጠበቀው በታች ቀጥራቸው ያነሰ ለመጭው ትውልድ ከልብ የተቆረቆሩ ሰዎች፣ የት/ቤቱ የቀድሞ ተመራቂዎች፣ የከተማው ተወላጆች፣ በተጨማሪም የጎንደር ህክምና ሳይንስ ኮሌጅ ተመራቂ ሀኪሞችና ጥቂት በጎ አድራጊዎች በውጭ ሀገር ባደረጉት የገንዘብ ርዳታና በሀገር ቤትም እንዲሁ በገንዘብና በቁሳቁስ በተደረገ ርዳታ ህንጻው ተጀምሮ አሁን በአይን የሚታይ ደረጃ ደርሷል፡፡
ሆኖም ይህ ከአራት አመታት በፊት የተጀመረው ሥራ፣ በወረርሽኙና በሌሎች ችግሮች ምክንያት በተጠበቀው ፍጥነት መሄድ እንዳልቻለ ግልጽ ነው፡፡ በዚህ ላይ ግን መካድ የማይቻል ያልተለመደ ነገር በዚህ ፕሮጀክት ላይ ታይቷል፡፡ አንደኛ ሰለ ት/ቤቱ መሠራት መረጃውን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እየተቀባበሉ ማየታቸው በግልፅ የታየ ነገር ነው፡፡ ለዚህ የሰዎች በዚህ ጉዳይ ላይ ድርሻቸውን ላለመወጣት በቂ ምክንያት ነው ባይባልም፣ ት/ቤቱ እንዳይሠራ፣ የከተማው ተወላጅ የሆኑ ግለሰቦች ያደረጉት አሉታዊ ቅሰቀሳ ሳይጠቀስ መታለፍ የለበትም፡፡ አንዱ ሙግት፣ “መንግሥት ያሠራው ለምን ታዋጣላችሁ” የሚል ቅስቀሳ ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ የተዋጣው ገንዘብ አይደርስም ለሌላ አገልግሎት እየዋለ ነው የሚል አሉባልታ በፊት ለፊትም ሆነ በውስጥ በግልፅ በመነገሩ ፕሮጀክቱን ለመርዳት ያሰቡ ሰዎች እጃቸውን እንደሰበሰቡ ይታወቃል፡፡ ሰለዚህ ፕሮጀክት ገንዘብ አሰባሰብና አጠቃቀም ግልፅና ህጋዊ በሆነ መንገድ እንደሚካሄድ በተደጋጋሚ በተገኙ መድረኮች ተገልጧል፡፡ የአሜሪካ መንግሥትም በየጌዜው ኦዲት የሚያደርገው ነገር ነው፡፡ አሁንም በግልጽ ለዚህ ጉዳይ በተዘጋጀው ድረ ገፅ ተዘርዝሯል፡፡
ጥያቄው፣ ይህ ፕሮጀክት አልቆ ተማሪዎች ዘመናዊ የሆነ ጥራት ያለው ትምህርት ቢያገኙና፣ ቢቻል የተሻለ ደረጃ አለዚያም ከሌሎች አካባቢ ተማሪዎች ኋላ እንዳይቀሩ ማድረግ ጉዳቱና ክፋቱ ምን ላይ ነው? ማንስ ነው የዚህን አካባቢ ውድቀትና ጥፋት የሚመኘው? ለሀገርና ለወገን መቆርቆር ትርጉሙ ምንድን ነው? ይህ ፕሮጀክት ቆሞ ቢቀርና መሳለቂያና መዘባበቻ ቢሆን ማንን ነው የሚያስደስተው? ቁጭት የሚባል ነገርስ የለም ወይ?
የተጀመረውን ህንጻ ያዩ ሰዎች፣ በመቆርቆርም ለማገዝ መፈለጋቸው ግልፅ ነው፡፡ አዳዲስ ሀሳቦች ሲዘነሩም እያየን ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክት ከጎንደር ከተማ ጀምሮ እስከ ውጭ ድረስ፣ ሥነ ሥርአት ያለው መዋቅርና፣ ህጋዊና ግልፅ የሆነ የገንዘብ አሰባሰብና አጠቃቀም ያለው ሂደት ያለው በመሆኑና፣ በተጨማሪም በሀገር ቤት፣ ከጎንደር ዩኒቨርስቲ መሀንዲሶች ጀምሮ፣ የፕሮጀክቱ አሰተባባሪዎች፣ ጊዜያቸውን ሰውተው በነፃ የዜግነትና የተቆርቋሪነት ግዴታቸውን እየተወጡ ያለበት ፕሮጀክት ነው፡፡ እንደውነቱ ከሆነ ርዳታ ለመስበሰብ፣ አስተባባሪው ቡድን ያላደረገውና ያልሞከረው ነገር የለም፡፡ ከቲኬት ሽያጭ ጀምሮ፣ ጨረታዎች፣ የዙም ስብሰባና ርዳታ ማሰባሰብ፣ የተለያዩ መሥሪያ ቤቶችን ርዳታ መጠየቅ፣ በተወሰኑ ከተማዎች የገንዘብ ርዳታ ስብሰባዎች ማድረግን ያካትታሉ፡፡ ዋነኛ የገንዘብ ማሰባሰቢያ መንገድ ሆኖ የተገኘው ደግሞ በጎፈንድሚ አካውንት ነው፡፡ ህጋዊ ለማድረግና፣ ለሚያዋጡ ሰዎች የታክስ ቅነሳ እንዲያገኙ በማሰብ በአሜሪካ መንግሥት በ501-C (non-profit) ደረጃ በተመዘገበው የፋሲለደስ መረደጃ ማህበር አካውንት ነው የምንጠቀመው፡፡ ጎፈንድሚ ምን ያህል ጥብቅ የገንዘብ አሰባሰብና አሠረጫጨት እንደሚከተል ማወቅም ተገቢ ነው፡፡ ሰለዚህ ጉዳይ በዝርዝር ለመመልክት ድረ ገፁን ይጎብኙ፡፡
በአሁኑ ወቅት ለተለያዩ ጉዳዮች ርዳታ የሚጠየቅበት ጊዜ በመሆኑ፣ ነገር ግን ይህ ፕሮጀክት ቀደም ብሎ የተጀመረ ሰለሆነም፣ በተለይም የተጀመረው ህንጻ በዝናብ ሆነ በፀሀይ ምክንያት ጉዳት ላይ ከመድረሱ በፊት በትህትናና በአክብሮት በጎንደር ከተማና በመጭው ትውልድ ሥም፣ የተቻለዎትን በመለገሥ የተቆርቋሪዎች ሥም ዝርዘር ውስጥ ራስዎን እንዲያስገቡ እንጠይቃለን፡፡ እንደ ብዛታችን አነስ ያለ መዋጮም አድርጎ በቁጥር ላቅ ያለ ርዳታ ቢደረግ ፕሮጀክቱ ግቡን ይመታል፡፡ በመሆኑም እያንዳንዳችን ባደረግነው ነገር ለራሳችንም ሆነ ለትውልድ መወሳት የሚችል የተቆርቋሪነትና የዜግነት ግዴታ መወጣት ይሆናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ርስዎ የሚችሉትን ካደረጉ ደግሞ ሌሎች የርስዎን አርአያ ተከትለው ይህ ፕሮጀክት ባጭር ጊዜ ውስጥ ግብ እንዲደርስ ማድረግ ደግሞ ታላቅ አስተዋፅኦ ነው፡፡ የሚችሉትን ለመለገሥ ወደ ጎፈንድሚ ቀጥታ መሄድ ወይም ደግሞ ወደ ድረ ገፁ በመሄድ ተጨማሪ መረጃዎችን በማንበብ ድረ ገፁ ውስጥ ያሉ የጎፈንድሚ ሊንኮችን ይጫኑ፡፡
Copyright © 2024 Fasiledes School Project - All Rights Reserved.
Powered by GoDaddy
We use cookies to analyze website traffic and optimize your website experience. By accepting our use of cookies, your data will be aggregated with all other user data.